Part 1
የዛሬው እንግዳችን የአላህ ባሪያ እና ነቢይ የሆነው ዒሳ ኢብን መርየም ቢንት ዒምራን ኢብን ማሳን ኢብን ጋዚር ኢብን አልዩድ ኢብን ኢክተር ኢብን ሳዱቅ ኢብን ኢያዙዝ ኢብን አልያቂም ኢብን አይቡድ ኢብን ዙርያቢል ኢብን ሻልታል ኢብን ዩሀይና ኢብን በርሻ ኢብን አሙን ኢብን ሚሻ ኢብን ሂዝቃ ኢብን አሀዝ ኢብን መውሳም ኢብን አዝሪያ ኢብን ዩዋርም ኢብን ዩሻፊጥ ኢብን ኢሻ ኢብም አይባ ኢብን ረህባዓም ኢብን ሱለይማን ኢብን ዳዉድ……በመባል የዘር ሀረጉ ከዳዉድ ይመዘዛል።
ትናንት እና ከትናንት በስቲያው እንደዳሰስነው መርየም በህፃንነቷ ለቤተ አምልኮ የተሰጠች ልጅ ስትሆን ዉሎ አዳሯ እዚያው ቤተ አምልኮ ውስጥ ነው።ለወሳኝ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከዚያ ግቢ አትወጣም ነበር።
ኢዚያ ቤተ አምልኮ ውስጥም ዩሱፍ የተባለ የአጎቷ ልጅ አለ።እሱም ውሎ አዳሩ እዚያው ስለሆነ ዝምድናቸውን ይበልጥ አጠናክሮታል።ዘወትር ውሀ ለመቅዳትም ከቤተ አምልኮው አቅራቢያ ወዳለው ምንጭም አብረው ነበር የሚሄዱት። ከእለታት አንድ ቀን መርየም እንስራዋን ይዛ ዩሱፍ ዘንድ በመሄድ፦”ምንጩ ጋ ሄደን ውሀ እንቅዳ” አለችው።
ዩሱፍም፦”እኔ እስከ ነገ የሚበቃኝ ውሀ አለኝ” አላት።
እሷም ትታው ብቻዋን ሄዳ ምንጩ ቦታ በመቅዳት ላይ ሳለች ጂብሪል በሰው ተመስሎ አጠገቧ ቆመ። እሷም በጣም ደንግጣ፦”አላህን የምትፈራ እንደሆን ካንተ በአላህ እጠበቃለሁ።” አለችው።
እሱም፦”እኔ ንፁሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ” አላት።
መርየምም፦”(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራም ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!?” በማለት ጠየቀች።
ጂብሪልም፦”(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው፡፡ ጌታሽ እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፡፡ ለሰዎችም ታምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው ብሏል አላት።
ያን ግዜ እሷም ለጌታዋ ትእዛዝ እጅ ሰጠች።ጂብሪልም ጠጋ አለ’ና ደረቷ ላይ ልብሷን ከፈት አድርጎ ሩህ ነፋባት።መርየምም በእንስራዋ ውሀዋን ሞልታ ወደ ቤተ አምልኮው ተመልሳ ሄደች።
ግዜ ግዜን እየተካ የመርየም ፅንስ ሆዷን እየገፋ መጣ።ይሄን የተመለከተውም የአጎቷ ልጅ ዩሱፍ ሁኔታው በጣም ግራ አጋባው።አርግዛ ነው እንዳይል ከቤተ አምልኮ ከሱ ውጭ ከማንም ወጥታም ታይታም አጣውቅም።ምንም አልተፈጠረም እንዳይል የእርግዝና ምልክቶች እንዳለ ይታዩባታል።
በመጨረሻም ይሄን የሚያጣራበት አንድ መፍትሄ አገኘ’ና ሊያናግራት ወስኖ እርሷ ዘንድ በመሄድ፦”መርየም የሆነ ነገር በውስጤ ይመላለሳል።እደብቅሻለሁ እያልኩ ግን አልቻልኩም በቃ ልጠይቅሽ” አላት።
መርየምም፦”መልካምን ንግግር ተናገር(ጠይቅ)” አለችው።
ዩሱፍም፦”ቡቃያ ያለ ዘር ይበቅላልን?” አላት።
መርየምም፦”አዎን ይበቅላል” አለችው።
ዩሱፍም፦”አረንጓዴ ቅጠልስ ዝናብ ሳያገኝ መብቀል ይችላልን?” አላት።
መርየምም፦”አዎን መብቀል ይችላል” አለችው።
ዩሱፍም፦”ያለ ወንድ ሴት ልጅ ብቻ መውለድ ትችላለችን?” አላት።
መርየምም፦”አዎን ትችላለች” አለችው። መርየምም ቀጠል አድርጋ፦” ዩሱፍ ሆይ! አላህ ቡቃየን የፈጠረ ቀን ያለ ዘር እንደፈጠረው አታውቅምን?!!
አላህ አረንጓዴ ቅጠልንስ ለመጀመሪያ ግዜ ሲፈጥረው ያለ ዝናብ እንደፈጠረው አታውቅምን?!!
ታዲያ መጀመሪያ ቅጠልን እና ቡቃያን ዘርም ሆነ ዝናብ ሳይኖር የፈጠረው ጌታ አሁን ያለ ዝናብ እና ያለ ዘር መፍጠር ይከብደዋል ትላለህን!!!?” አለችው።
ዩሱፍም፦”አይ እኔ እንደዛ ልል ፈልጌ አይደለም አላህ በፈለገው ነገር ላይ ሁሉ ቻይ ነው።አንድን ነገር ማድረግ በፈለገ ግዜም ሁን ይለዋል ይሆናልም” አላት። መርየምም፦”አላህ ያለ ወንድም ሆነ ያለ ሴት አደምን አልፈጠረምን!!!? ያለ ሴትስ ሀዋን አልፈጠረምን!!!?” አለችው።
ዩሱፍም፦”አዎን ፈጥሯል” አላት። ከዚያም በልቡ ግን መናገር ያልፈለገችው ያአላህ ተአምር በሆዷ እንዳለ አወቀ።
መርየምም የመውለጃ ሰዐቷ በተቃረበ ግዜ የቤተ አምልኮውን ግቢ ለቃ ወጣች።ብቻወን በረሀ ላይ ሳለች ምጡ ጀመራት በጣምም አመማት አሁን ያለችበትን እንግልት እና ከመውለዷ በኋላ የሚከተላትን እንግልት ስታስብ፦”ዋ! ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ፡፡ ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ” ብላ ተመኘች።
በመጨረሻም ወደ አንድ የደረቀ የተምር ዛፍ ዘንድ በመጠጋት ልጇን ዒሳን ተገላገለች።ልክ ልጁን እንደተገላገለች ጂብሪል መጣ’ና፦” አትዘኝ፡፡ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል፡፡
የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና፡፡ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም” አላት።
በልታ ስታበቃም ጂብሪል፦”ማንም ሰው ሊያናግርሽ ቢፈልግ እኔ ለአር ረህማን(ለአላህ) ማንንም ሰው ላላናግር ፆሚያለሁ በይ” አላት።
ኢብሊስም መርየም ልጇን ከተገላገለች በኋላ ወደ ኢስራኢላውያኑ ካህናት በመሄድ የመርየምን መውለድ ነገራቸው።ካህናቱም በጣም በመቆጣት ይዝቱባትም ጀመሩ።
ከዚያም መርየም ልጇን ተሸክማ ወደ ቤተ አምልኮው መጣች። ሁሉም ተሰብስቧል….ገና ፊትለፊታቸው ብቅ ስትል፦”የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፡፡ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም” አሏት።(የሀሩን እህት ያሏት ሳሊህ ሰዎችን በሀሩን ስለሚመስሉ ነው።)
እሷም ምንም መልስ ሳትሰጥ ህፃኑን እንዲያናግሩ ወደ ልጇ አመላከተቻቸው።ሁሉም በሁኔታዋ በመገረም ዚና ያደረገችው እንሷት እኛ ላይ ታሾፋለች እንዴ እያሉ ከተነጋገሩ በኋላ፦”በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን” አሏት።
ያን ግዜ ህፃኑ ዒሳ ቀና በማለት፦”እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፡፡ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል።
በየትም ስፍራ ብሆን ብሩክ አድርጎኛል፡፡ በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል፡፡ ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)፡፡ ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም።
ሰላምም በእኔ ላይ ነው፡፡ በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን” ብሎ ተናገረ።
ይህን የህፃኑን ንግግር በሰሙ ግዜ ሊወግሯት ተሸክመው የመጡትን ድንጋይ ይዘው ተመለሱ።
የአላህ ፍቃድ ሆኖ ዒሳ አድጎ ከህፃናት ጋር በመንገድ ላይም ለመጫወት በቃ።
ከእለታት አንድ ቀን ዒሳ ከአከባቢው እኮዮቹ ጋር በመጫወት ላይ ሳለ አንድ ህፃን ሌላኛውን ህፃን በእግሩ ገፍትሮ ሲጥለው ህፃኑም የዒሳ እግር ስር ወድቆ ሞተ።
ሰዉ ሲሰበሰብ ሟች ህፃኑን በዒሳ እግር ስር ወድቆ ተመለከቱ።የህፃኑ ገዳይ ዒሳ ነው በማለትም ዒሳን በጨቅላ እድሜው ለፍርድ አቀረቡት።
ዳኛውም፦”ህፃኑን ገድለሀልን?” ብሎ ሲጠይቀው ዒሳም፦”አልገደኩትም” አላቸው።ከዚያም ዒሳን ለቅጣት ዚያዘጋጁት ዒሳም ለዳኛው፦”እሺ የሞተውን ህፃን አምጡልኝ” አለ።
ዳኛውም በዒሳ ሁኔያ በመገረም የህፃኑ አስክሬን እንዲቀርብ አዘዘ’ና ዒሳ ፊትለፊት ላይ ቀረበለት። ዒሳም ዱዓ ሲያደርግ አስክሬኑ በአላህ ፍቃድ ህያው ሆነ።ከዚያም አስክሬኑን፦”ማን ገድሎህ ነው?” ብለው ሲጠይቁት፦”ኤኬሌ…ነው” ብሎ የገዳዩን ልጅ ስም ጠራላቸው። ዳኞቹም፦”የዚህስ ልጅ ስሙ ማን ይባላል” ሲሉት፦”ዒሳ” ብሎ መለሰላቸው። አስክሬኑም ይህን እንደተናገረም ተመልሶ ሞተ።የዒሳም ንፁህነቱ ተረጋግጦለት ተለቀቀ።
ዒሳም በህፃን አንደበቱ እንዲህ ሲል አላህን ያወድስ ነበር፦”አላህ ሆይ! አንተ ከከፍታህም ጋር ቅርብ ነህ። ከመቅረብህም ጋር የላቅህ ነህ። ከፍጥረታትህ ሁሉም የበላይ ነህ። አንተ ያ… ሰባት ሰማያትን በሀዋእ ላይ የፈጠርክ ነህ።